ኮሮና-
ና! አለኝ
ከመንገድ ላይ ሲያየኝ
ሰነፍ መሆኔን ሊፈትሸኝ
እንድጠጋው…… እንዲጠጋኝ
ትንፋሼን ከስትንፋሱ ሊያገናኝ
እንደገና ጠራኝ ና! …አለኝ
አውቅኩበት …ፈራሁት
… በሩቁ ሸሸሁት
የሩቁን አስታወስኩት
…………ያን ሽውታ
………የህዳር በሽታ

እንዲህ ሲል ግን ሰማሁት
ኮሮና

ከንቱ ናቸው ለኔ
ጽድቅ እና ኩነኔ
አይምጡብኝ እንጂ ከመጡ ወደኔ
ከተገጣጠምን ከደረስኩባቸው
ከተሰነቀርኩኝ ከስትንፋሳቸው፣
አይቀርላቸውም መስቃየታቸው
ለኔ ደስታ መፍጠር ትቢያ መሆናችው
ሲል ሰማሁት
አስደነገጠኝ አሁንም ፈራሁት

እንደገና ጠራኝ
ና ! አለኝ
ጠረጠርኩኝ
እንዳይዘኝ
እንዳያገኘኝ
ሩጫ ጀመርኩኝ

ግን
ኮሮና … ይጮኃል

ሰማሁት እንዲህ ሲል

…ግራ ቀኝ ሳልል
…ገነት ይሁን ሲኦል
…ዳርም ሆነ መሀል
…ካገኝሁ ስትዋልል
እኔን አያድርገኝ
ይዘህ ከጨበጥከኝ
ቀርበህ ካዋራኸኝ
ምንም የማትለየኝ
መቼም የማታውቀኝ
ግን የማታመልጠኝ
እኔ ኮሮና ነኝ
አለኝ

ሰቀቀኝ
የሰው ዘር ሊጨርስ የመጣ መሰለኝ
ሲያባርረኝ ስሮጥ ሲከተለኝ
ከቤቴ ገብቼ ዘግቼ አመለጥኩኝ::

ሳዳምጠው……በቀዳዳ ሳየው

ይቦርቃል፥ ያቅራራል ፥ይፎክራል
ምድርም አልበቃችው አየር ላይ ይበራል
ሲያቅራራ እንዲህ ይላል፣
…………እኔ ኮሮና ነኝ ጀቱ
…………ኮረንቴ መብራቱ፣
አያስጥላችሁም ዘር ጎሳ ኃይማኖቱ፣
የዓለም መሪነቱ ኃያል ነኝ ማለቱ
ወጣት አዛውንቱ ሐብት ድህነቱ
አያስጥላችሁም ……
አይቀርላችሁም አንድ ናችሁ ለኔ
ሳብ ማግ አድርገው ካለፉ ከጎኔ
ከተገጣጠምን ከመጡ ወደ እኔ
ዋዛ እንዳልመስላችሁ፣
አይቀርላቸሁም ትቢያ መሆናችሁ

ይላል ይፎክራል ሁኔታው ያስፈራል
እኔም ያን አይቼ
ከሚሉት ሰምቼ
ከቤቴ ከትቼ
እለምናለሁ ፈጣሪን
እባክህ መድሐኔቱን ልቀቅልን
በዝቶ እንጂ ኃጤያታችን
ሳይሆን አይቀር መድሐኔቱ በእጃችን
ትዝብት ውስጥ ነን እያንዳዳችን

ስለዚህ ወገኔ በመሬት ላይ ያለህ
ካልሰማህ ልንገርህ
ትንፋግ ነው ኮሮና አይታይም በዓይንህ ልምጥማጭ ነውና
የት እንደሚያገኝህ አታውቀውምና
ተጠንቅቀህ እለፍ ሁሉን ጠርጥርና
እቤትህ ተቀመጥ በርህን ዝጋና
የተሻለው ጊዜ እስኪመጣ ድረስ
ፈጣሪን ተማጸን ጸሎትህን አድርስ
ከዛስ ?
ከዛማ
ከተባበርን…ከተረዳዳን…ከተጠነቀቅን
ይመጣል ጥሩ ቀን::

ከአቅራቢ
ሚያዚያ 03/2012

Share to friends
Shopping cart
There are no products in the cart!
Continue shopping
0